የታጠቁ ሀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ ነው-ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
የታጠቁ ሀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ ነው-ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ጥር 2 /2017(ኢዜአ)፦የታጠቁ ሀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የለውጡ መንግሥት መምጣትን ተከትሎ በሀገርና ህዝብ ሀብት የግል ጥቅማቸውን ማጋበስ ያልቻሉ ሀይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ሲቀሰቅሰሱ ይስተዋላል፡፡
በዜጎች የዘመናት ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች ሥም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጫካ የገቡ ሀይሎችም ብዙ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ፍላጎትን በሀይል ማሳካት እንደማይቻል የተገነዘቡ ወገኖች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ትግል መመለስ ጀምረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች የሰላም ጥሪ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በተለያዩ መድረኮች የሰላም አማራጮችን ለሚከተሉ ሀይሎች በሩ ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ማረጋገጡን ገልጸው፥ችግሮችን በውይይት መፍታት አትራፊ የሚያደርገው ሀገርን መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለዚህም የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የታጠቁ ሀይሎች የመንግሥትን ጥሪ መቀበላቸውም በግጭት የሚጎዳ እንጂ የሚያተርፍ አካል እንደሌለ በመረዳታቸው ነው ብለዋል፡፡
ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊ ውይይት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በትጥቅ ትግል የሚሳካ የትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት እንደሌለ ተናግረዋል።
የሀገራቸውንና ህዝባቸውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የቆረጡ ሀይሎች ከመንግሥት ጋር መነጋገርን ምርጫቸው ያደረጉ ሀይሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ ሀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ክልሎች ትጥቅ አንስተው የነበሩ ሀይሎች የሰላም ጥሪውን መቀበላቸው መንግሥት ለሰላም ያለውን ዝግጁነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የታጠቁ ሀይሎች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ማመናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም ለሁለቱም ወገኖች ለሰላም ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያሳይ በመሆኑ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡