የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት የማስከበሩን ተግባር በጥናትና ምርምር እናግዛለን- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት የማስከበሩን ተግባር በጥናትና ምርምር እናግዛለን- ምሁራን
አዳማ፥ጥር 2/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሰላም በዘላቂነት የማስከበሩን ተግባር ለማረጋገጥ አስፈላጊው ጥናትና ምርምር በማድረግ እንደሚያግዙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ በብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና በአገር ግንባታ ጉዳይ ዙሪያ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምሁራኑም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥና በአገር ግንባታ ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር በተሰማራንበት ሙያ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን አለሙ (ዶ/ር)፤ ''ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር አሁን እንደ አገር ካሉብን ችግሮች ለመውጣት ወሳኝ ነገር ነው'' ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ምሁራን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራንም እያገዙ መሆኑን አመልክተው፥ ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥና ለአገራዊ መግባባት የሚያግዙ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብም አስረድተዋል።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ታረቀኝ አብረሃ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በአገራችን ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር በተለይ ከምሁራን ብዙ ይጠበቃል።
ለዚህ ደግሞ የህዝቦች ትስስርና አንድነት የሚያጠናሩ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ሲሆን፤ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥም ጥናትና ምርምሮችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ በሰይፍ ጥሩ (ዶ/ር) የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በተለይ ምሁራን የሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
አገራዊ ጥቅማችንን በመለየት የማህበረሰብ አመለካከትና አስተሳሰብ ከመቅረፅ ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ እንደሚያተኩሩ አስረድተዋል።
አገራዊ ማንነትና ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊጎዱ የሚችሉ የውስጥ ችግሮቻችንና አለመግባባቶችን በመፍታት ላይ በትኩረት መስራት አለብን ነው ያሉት።
በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ መግባባት ዴስክ ሀላፊ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሊሂቃን ሚና ወሳኝ በመሆኑ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገራዊ ጉዳይ በመለየት በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ልሂቃን ጋር በጥምር ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።