ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፤ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የፍትህ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር የስራ ዘርፍ ኃላፊ ዩዋን ሊያንግ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ነው።

ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን በሁኔታዎች የማይለወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት (all-weather strategic partnership) በውይይታቸው አጽንኦት ሰጥተው ተወያይተውበታል።

አምባሳደር ተፈራ፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና በህዝብ ለህዝብ፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ቱሪዝምን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።

የቻይና የፍትህ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር የስራ ዘርፍ ኃላፊ ዩዋን ሊያንግ፥ የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነት የሚደነቅ ሲሉ ገልጸዋል።

ኃላፊው የቻይና የፍትህ ሚኒስትር ሂ ሮን እ.አ.አ ፌብሩዋሪ ወር አጋማሽ 2025 በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በዚሀም ተቋማቱ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አምባሳደር ተፈራ መንግስት፥ በቻይና ፍትህ ሚኒስትር የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ለሚያደርገው ጉብኝት ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የልዑኩ ጉብኝት እያደገ በመጣው የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ሲል በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመረጃው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም