እስራኤል የኢትዮጵያን ግብርና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
እስራኤል የኢትዮጵያን ግብርና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፤ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የግብርናን ምርታማነት ለመጨመር እያከናወነች ያለውን ተግባር በቴክኖሎጂ በመደገፍ ትብብሯን የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ እስራኤል ገለጸች።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያና እስራኤል በምጣኔ ሃብትና ህዝብ ለህዝብ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት የተጠናከረ ነው ።
ሁለቱ አገራት ያላቸውን ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በምጣኔ ሃብትና ልማት የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
እስራኤል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጠብታ መስኖ ምድረ-በዳን ወደ አረንጓዴነት መቀየር የቻለችበትን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለም አፈር ላይ ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን ለመጨመር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቀደም ሲል የተጀመሩና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን መስኖ ልማት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደምትሰራም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
ለዚህም በህዳር ወር 2017 ዓ.ም ኢኖቬሽን፣ ጤና እና ማዕድንን ያካተተ የእስራኤል ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ አማራጮችን መመልከቱን አስታውሰዋል።
የእስራኤል ባለሃብቶች በነበራቸው ቆይታ በኢኖቬሽንና በግብርና ቴክኖሎጂ፣ ማዕድንና ሌሎች ዘርፎች የመስራት ፍላጎት እንዳሳዩም ጨምረው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ ያመቻቻቸውን አስቻይ ሁኔታዎች የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በተመሳሳይ የእስራኤል ባለሃብቶች በአቮካዶ ምርት የጀመሩትን ኢንቨስትመንት የበለጠ የማስፋት ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ እስራኤል የኢትዮጵያን ቡና፣ ሰሊጥና ጤፍ በስፋት የምትጠቀም በመሆኗ የግብርና ምርታማነት መጨመር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው።
ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ ኢትዮጵያ በጸሃይ፣ ንፋስ እና እንፋሎት ያላትን የታዳሽ ሃይል አቅም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመስኖ ልማት ለማዋል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእውቀት ሽግግር በማድረግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
እስራኤል እና ኢትዮጵያ በህክምና ዘርፍ የቆየ ትብብር ያላቸው ሲሆን በቅርቡ የመጣው የእስራኤል የህክምና ቡድን የአይንና የልብ ህክምና መስጠቱን በማስታወስ ተግባሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።