የኢትዮጵያ ፖስታ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር መጠቃለሉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው- ዳግማዊ ሀይሊዬ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖስታ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር መጠቃለሉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው- ዳግማዊ ሀይሊዬ
አዲስ አበባ፤ጥር 2/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፖስታ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር መጠቃለሉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳግማዊ ሀይሊዬ ተናገሩ።
በቅርቡ ስምንት ተጨማሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ደግሞ አዲስ ከተቀላቀሉ የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳግማዊ ሀይሊዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በስሩ ያሉት የልማት ድርጅቶች በኢንቨስትመንት የበለጠ ውጤታማ ሆነው እንዲሰሩ የሚያግዝ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኩባንያዎቹን ውጤታማነት በማስቀጠል ለሀገር የተሻለ ጥቅም እንዲያበረክቱ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ተቋሙ ቀደም ብሎ የሪፎርም ስራዎች መጀመሩን አስታውሰው፥ አሁን ያገኘው ዕድል የያዘውን የለውጥ ምዕራፍ ለማሳለጥ እንደሚያግዘው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ እንደ ተቋም ከ2016 ዓም ጀምሮ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ተቋሙ ባገኘው ዕድል በመጠቀምና አሰራሩን ከኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስትራቴጂ ጋር በማገናኘት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዘው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትርፋማ እንዳልነበር የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ትርፋማ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የተቋሙ ለውጥ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ተቋማዊ አሰራሮች የሚገለጽ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ስትራቴጂዎች ለይቶ በማስቀመጥ በሁሉም ዘርፍ መሻሻሎች መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም አዳዲስ ተሞክሮዎችንና አሰራሮችን በመቀመር ለሀገር የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።