ቀጥታ፡

በርዕደ መሬቱ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከ58 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ገብተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦ በርዕደ መሬቱ ሳቢያ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከ58 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ በማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ በአፋር ሁለት ወረዳዎችና በኦሮሚያ ክልል አንድ ወረዳ ያጋጠመውን ርዕደ መሬት በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በስብሰባው የዘርፉ ምሁራን ባቀረቡት ሳይንሳዊ ትንታኔ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ርዕደ መሬቶች በአመዛኙ ከስምጥ ሸለቆ አፈጣጠር ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እስከ አሁን ባጋጠሙ ርዕደ መሬቶች የምድር ውስጥ ጭስ እና ፍል ውሃ እንጂ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እንዳልተከሰተ ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ የስምጥ ሸለቆ አካል በሆኑ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ፈንታሌ፣ በአዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች የተከሰተው ርዕደ-መሬት፣ የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታና የንዝረት አደጋ ስጋቶች ልዩ ትኩረትና ምላሽ የሚሹ ናቸው።


 

ክስተቱ በተለይም በጂኦግራፊያዊ ስፋት፣ በድግግሞሽና በመጠን እየጨመረ መሄዱ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሂደት የዜጎች ሕይወት እንዳይቀጠፍ፣ ንብረት እንዳይወድም፣ መሰረተ-ልማቶች እንዳይጎዱና የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እንዳያስከትል የቅደመ አደጋ ጥንቃቄ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአደጋ ስጋት ቦታዎች ለሚነሱ ወገኖች ተገቢውን መጠለያና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

እስከ አሁን የጠፋ የሰውና እንስሳት ሕይወት ባይኖርም በማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት፣ በመንገዶችና በከሰም ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ ላይ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጽ ጉዳትና ውድመት መድረሱንም አንስተዋል፡፡

የፌዴራልና የክልል ተቋማት በቅንጅት የአደጋ ምላሽ ተግባራትን እያከናወኑ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጋር አካላትም የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ርዕደ መሬቱ በአፋር አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አደጋና ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ከ74 ሺህ በላይ የህብረሰተብ ክፍሎች ውስጥ ከ58 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።


 

የምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍም በተጠናከረ መልኩ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) በአስቸኳይ ስብሰባው ምሁራን ስለ ርዕደ መሬቱ ስጋት ባቀረቡት ትንተና ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በዚህ መሠረትም የስጋት ቀጣና በሆኑ አካባቢዎች የተቀናጀ የአደጋ ምላሽ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የተግባቦት ሥራውም ህብረተሰቡን የሚያሳውቅና የሚያስገነዝብ ሆኖ የተናበበ መረጃን ከአንድ ማዕከል ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ከሚመለከተው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ከሙያተኞች የሚሰጡ መረጃዎችን በአግባቡ እንዲከታተል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም