ቀጥታ፡

ርዕደ መሬቱን ተከትሎ በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገምግመናል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦ በስምጥ ሸለቆ የተከሰተውን ርዕደ መሬቱን ተከትሎ በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ዛሬ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የርዕደ-መሬት ክስተት በተመለከተ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደናል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት በአስቸኳይ ስብሰባችን የሳይንስ ማህበረሰቡ አካላት እና የሁለቱ ክልሎች አመራሮችም እንዲሳተፉ አድርገናል ነው ያሉት።


 

ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል በሆኑ አካባቢዎች የተከሰቱ የርዕደ-መሬትና ንዝረት ስጋቶች በልዩ ትኩረት መከታተል የሚገባን መሆኑን ተግባብተናልም ብለዋል፡፡

የክስተቱ ድግግሞሽ እና ስፋት በአካባቢው በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን መገምገሙን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራልና የክልል መዋቅሮች የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ምላሽ እየሰጡ መሆኑን እና የሳይንስ ማህበረሰቡ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለ መረጃ የሰጠ መሆኑን እንደተመለከቱም ገልፀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል አጋር አካላት እና የሚመለከታቸው ሴክተሮች የቅድመ መከላከል ስራውን በትኩረት ደግፈዋል ነው ያሉት።


 

በአስቸኳይ ስብሰባችን የርዕደ- መሬት ክስተቶችና የተሰጡ ምላሾችን በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች እና ተግባራት ላይ አቅጣጫ እንደተቀመጠም ጠቁመዋል።

እስካሁን በቅድመ መከላከል ውጤታማ ስራው ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም