የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ለዜጎች ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ለዜጎች ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ነው
አዲስ አበባ፤ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ለዜጎች ወጥነት ያለው እና ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን ማጽደቁ ይታወቃል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የጸደቀውን የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ መንግስት የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ እስትራቴጂዎችን እና መመሪያዎችን በማውጣት ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊ እና ተደራሽነትን ባረጋገጠ መንገድ የዜጎችን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የጤና ፖሊሲ መነሻ በማድረግም የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን አውስተው ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
አዋጁ ለዜጎች ወጥነት ያለው እና ዘመኑን የዋጀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም አዋጁ በጤናው ዘርፍ ያሉ ህጎችን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ እና በሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰጡቱ አገልግሎቶች ግልጸኝነት እንዲኖራቸው ከማገዝ ባለፈም የጤና ባለሙያዎችን ሃላፊነት በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም ህበረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አዳዲስ የጤና አገልግሎቶች ከቴክኖሎጂ ጋር በተጣጣመ መንገድ ለመስጠት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የጸደቀው አዋጅ በዋናነት በውስጡ ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የሴቶችና ህጻናት ጤና እንክብካቤ፣ የልብና የመተንፈሻ አካላት አሰራር ስርአት እንዲሁም የደም ህዋስ የአካል ክፍል ወይም የአካል ልገሳ ንቅለ ተከላ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዋጁ ማንኛውም ወላጅ፣ አሳዳጊ ወይም በህግ ሀላፊነት የተጣለበት ሰው ህጻናትን የማስከተብ ግዴታ እንዳለበት እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ ማግኘት ወይም ወላጅ መሆን ያልቻሉ በባለሙያ የተረጋገጠ ባለትዳሮች በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ ከራሳቸው በተገኘ የዘር ፍሬ ልጅ ማግኘት የሚችሉበትን አማራጭ የሚያስቀምጥ እንደሆነም አክለዋል።
ሌላኛው በአዋጁ ከተካተቱት ውስጥ የልብ እና የመተንፈሻ አካላት የአሰራር ሥርዓት መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ በመሳርያ ላይ የተመሰረተ የአተነፋፈስ ስርዓትን በሶስት አግባነብት ባላቸው ባለሙያዎች ውሳኔ ማቋረጥ የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያስቀምጥ ነው የተናገሩት።
ይህ ድንጋጌም ዝርዝር አፈጻጸም ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን እንደሆነም ተናግረዋል።
ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው አካል ፊት ቀርቦ በሚሰጠው ፈቃድ መሰረት ደም፣ ህዋሱን፣ ህብረ ህዋሱን፣ የአካል ክፍሉን፣ አካሉን መለገስ እንደሚችል አወጁ ይደነግጋል ብለዋል።
ይህም ሊሆን የሚችለው ይህን አገልግሎት ለመስጠት ሃላፊነት በሚሰጠው ተቋም ብቻ መሆኑን ነው የጠቆሙት ፣ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው በሽያጭ ወይም ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ደም፣ ህዋስ፣ ህብረ ህዋስን፤ የአካል ክፍል እና አካልን መለገስም ሆነ መቀበል እንደማይችልም ድንጋጌው ያስቀምጣል ሲሉ ሚኒስትሯ አብራርተዋል።