ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል - ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል - ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ ለበለጠ ውጤታማነት እድል እንደሚፈጥር የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
በቅርቡ ስምንት ተጨማሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀላቸው ይታወቃል።
አዲስ ከተቀላቀሉ የልማት ድርጅቶች መካከል ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አንዱ ነው።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን ኢንቨስትመንት በማስፋት የተወዳዳሪነት አቅሙን እንደሚያሳድግለት ገልጸዋል።
ዕድሉ ተጨማሪ ፓርኮችን በመገንባት ኢንቨስትመንትንና ንግድን ለማስፋፋት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት የተቀናጀ መሰረተ ልማትን ለኢንቨስተሮች በማቅረብ ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ መሰረተ ልማቶችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የነበረው ሂደት ያለውን ሀብት ወደ ስራ ማስገባት ላይ ያተኮረ እንደነበርም አንስተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ያገኘው ዕድል ተጨማሪ መሰረተ ልማትን በመገንባትና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ የበለጠ አትራፊ ሆኖ ለመዝለቅ ጥሩ እድል የሚፈጥርለት መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንቨስተሮች ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ጋር ተያይዞ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር በመፍታትና የውጭ ንግድን በማበረታታት ትልቅ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።