ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶችን መንግስት እየተከታተለ ርምጃ ይወስዳል - ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶችን መንግስት እየተከታተለ ርምጃ ይወስዳል - ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017 (ኢዜአ)፦ መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶችን እየተከታተለ ርምጃ እንደሚወስድ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አሳሰበዋል።
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት እንደ ዓለም አቀፉ የፔትሮል ዋጋ መረጃ የጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የአለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1ነጥብ 25 የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሸጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ አለው ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በኬንያ 1.351፣ በሩዋንዳ 1.136፣ በኡጋንዳ 1.299፣ በታንዛንያ 1.127፣ ማላዊ በ1.459፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 1.746 እንዲሁም በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባር ተጠምደዋል ነው ያሉት።
እነዚህ ባንዳዎች የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም፤ ራሳቸውን ለህዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለህዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉም ብለዋል።
ይህን የሚያደርጉት እውነታውን ስለማያውቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንዳይገለጥ ነው ያሉት ሚንስትሩ፤ ተሳስተው እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለው በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በህብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንደማያነሱ ገልፀዋል፡፡
ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጠራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን ስለሚጠይቅ ነው፤ እነሱ ይህ የላቸውም ብለዋል።
በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቸው አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጠል እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው፤ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነው፤ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግስት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በነጻ ገበያ ውስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ሥርዓት መንግስት እንዲያደርግ የማይገደድባቸው ጉዳዮችን በማንሳት መንግስትን ይከሳሉ፡፡ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም ብለዋል።
መንግስት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል፤ በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል፤ ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የህብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ ይሠራል፤ ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ይረዳል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድሃኒትና መሰል የጤና ጉዳዮች በዓመት ከፍተኛ የሚባለውን ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው። የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ስራም ተጀምሯል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን መንግስት በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
መንግስት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው፤እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል በማለትም አሳስበዋል።