ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን በኩራት እንናገራለን -ካዴቶች

አዲስ አበባ፤ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን በኩራት እንናገራለን ሲሉ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራቸውን በጎ ገጽታ ለመገንባት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠኑ ካዴቶች ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራቸውን በጎ ገጽታ ለመገንባት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠኑ ካዴቶች የተለያዩ የልማት ስራዎችን አስጎብኝቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሰጡት ማብራሪያ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የብሔረ ቤተ መንግሥት እድሳት፣ የአንድነትና ወዳጅነት ፖርኮች እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነት የአንድነት ፖርክ ዛሬ ውብና የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ከመሆኑ በፊት ለእይታ የማይመች የቆሻሻ መጠራቀሚያ ቦታ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የዲጅታል ዲፕሎማሲ ማሳያ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ለዓመታት በባለሀብት ታጥሮ የቆየ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ካዴቶች በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን የሚገልጹ ፕሮጀክቶች መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣በዲጅታል ቴክኖሎጂ፣በታሪካዊ ቅርሶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች መሆኗን ተረድተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም አንገታችንን ቀና አድርገን መናገር የምንችልበት ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን በኩራት እንናገራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም