ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሁነኛ አማራጭ ነው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሁነኛ አማራጭ ነው- ምሁራን
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ሀገራዊ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በውይይትና በምክክር ሂደት ዘላቂ ዕልባት ለመስጠት የሚያስችል ሁነኛ የመፍትሔ አማራጭ እንደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች ገለፁ።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሀገራዊ መግባባትና አንድነትን ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የምክክር ሂደቱ በስኬት እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ የምክክር ሂደት ተሳትፎና አስፈላጊነት ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ ለችግሮች ሁሉ ሁነኛ መፍትሄው ምክክር በመሆኑ የተጀመረውን የምክክሩ ሂደት ሁሉም ሊደግፈውና ሊያበረታታው ይገባል ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ ለሀገር ዘላቂ ሰላም መፍትሄ የሚያመጣና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የነቃ ተሳትፎና ትብብር በማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አንስተዋል።
የባህልና ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወሳኝ የተባሉና ለሀገር ዘላቂ ጥቅም እና አንድነት የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በውይይት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል ተስፋ የተሰነቀበት መሆኑንም አንስተዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፤ በበኩላቸው ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ የሚመጣበት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።
በየትኛውም መልኩ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች በመነጋገር መተማመንና መፍትሄ ማምጣት እንደሚችሉ ፅኑ እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ምሁራኑ አንስተዋል።
በተለይም የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ለዕርቅና ሰላም አበክረው መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አማራጮች የሚሰሩ ሁሉ ከምንም በላይ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስቀደም ለሰላም ቀናዒ እሳቤ ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በእስካሁኑ ሂደት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን በስኬት ቀጥሎ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ መሆኑ ይታወቃል።