ቀጥታ፡

አሚኮ የሚዲያ ኢንዱስትሪው የልህቀት ደረጃ ለመድረስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው - አቶ ይርጋ ሲሳይ

ባህርዳር፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፡- የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ) የሚዲያ ኢንዱስትሪው የልህቀት ደረጃ ለመድረስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪና የአሚኮ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።


 

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያስገነባው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንደገለጹት፤ አሚኮ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል በተሞክሮ ልውውጥና አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

በዚህም በክልሉ የሚካሄደው የኢንዱስትሪ፣ የግብርናና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑና የህዝቡ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል።

የተሳሳቱ ትርክቶች ታርመው ህብረ ብሔራዊነት እንዲሰርጽ ሁሉንም ያሳተፈ ውይይትና ክርክር በማካሄድ በህዝቦች መካከል መግባባት እንዲፈጠር የጎላ ሚና መወጣቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ በማጠናከርና የዘመኑ የሚዲያ ኢንዱስትሪ የደረሰበትን መረጃን በጥራትና በፍጥነት የማሰራጨት ተግባር ለማከናወን ያስገነባው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም የአሚኮ የሪፎርም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣ የአሚኮ የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አህመዲን መሃመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አሚኮ የዘመኑን የሚዲያ ውድድር መቀላቀሉን የሚያረጋግጥ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም "ወደ ቴክኖሎጂ ልህቀት" በሚል አሁን ላይ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ማስገባትና ተደራሽነት፣ በመረጃ ቅልጥፍናና ጥራት ላይ እያደረገ ያለውን ጥረት በመጥቀስ አመላክተዋል።

የሚዲያ ኢንዱስትሪው ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነበት በዚህ ዘመን ኮርፖሬሽኑ በየጊዜው አሰራሩንና አደረጃጀቱን በማዘመን ለክልሉ ብሎም ለሀገር ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም አሚኮ ሰላምን ማፅናት ላይ ትኩረት በማድረግ ታጣቂዎች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ የበለጠ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።


 

አሚኮ ከ30 ዓመት በፊት በበኩር ጋዜጣ ስራ ጀምሮ አሁን ላይ በሰባት ራዲዮና ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማሰራጨት የበቃ ድርጅት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአሚኮ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ናቸው።

በዚህም የክልሉን ብሎም የሀገሪቱ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ በመረጃ ልውውጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ በሁሉም ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ያስመረቀው ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች መረጃን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።


 

አሚኮ ያስገነባው የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ስቱዲዮ በሀገራችን ሶስተኛው ሚዲያ ያደርገዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ናቸው።

ይህም መረጃዎችን ለዓለም ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለስልጣኑ ለሚዲያው እድገት አጋዥ ተግባራትን በማከናወን የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም