የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርአት አዋጅ ዘመናዊ አሰራርን በማጠናከር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው - የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርአት አዋጅ ዘመናዊ አሰራርን በማጠናከር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው - የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ)፡- የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርአት አዋጅ ዘመናዊ አሰራርን በማጠናከር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስርአት አዋጅን አስመልክቶ ከንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል።
አዋጁ መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገባቸው የነዳጅ ውጤቶች ላይ የሚፈጸም ህገ-ወጥ ተግባርን በማስቀረት የህግ-ተጠያቂነትን ለማስፈን የነበረውን ክፍተት የሚሞላ ነው።
የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ በአዋጁ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ዝርዝር ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል።
ከነዳጅ ውጤቶች ጋር ተያይዞ የነበረውን የህግ ክፍተት የሚሞላ እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያጠናክር መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ከአስመጪው እስከ ተጠቃሚው ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ አስተማማኝ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአቅርቦት፣ ስርጭትና የችርቻሮ የአሰራር ስርአትንም ይዘረጋል።
የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ማከማቸት፣ ከግብይት ስርአት ውጪ መሸጥ፣ ወደ ጎረቤት ሀገራት በኮንትሮባንድ ማጓጓዝና ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራትን መፈጸም የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ተደንግጓል።
የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ አዋጁ ዘመናዊ አሰራርን በማጠናከር የነዳጅ ግብይትን የሚያዘምኑ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ፣ ፍትሃዊነትን የሚያሰፍኑና ሌሎች አሰራሮችን የሚዘረጋ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ500 በላይ የሚሆኑ ወረዳዎች የነዳጅ ማደያዎች የሌሉባቸው መሆኑን ተከትሎ በጥናት ላይ ተመስርቶ ፍትሃዊ የነዳጅ ማደያ እንዲኖር አዋጁ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ፍትሃዊ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር የሚያደርግ፣ ህገ-ወጥ አሰራርን የሚያስቀር፣ ዘመናዊ አሰራርን የሚዘረጋ፣ የነዳጅ ማደያዎች ግንባታ ተደራሽነትን የሚያሰፋ እንደሆነም ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስቶ በዝርዝር ተወያይቶ በ1 ድምጸ ታተአቅቦ በ2 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።