ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ሲሰለጥኑ የቆዩ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች ተመረቁ

 

አዲስ አበባ፤ጥር 1/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ሲሰለጥኑ የቆዩ 8ኛ ዙር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች ተመረቁ።

ተመራቂዎቹ በሁለቱ ተቋማት ትብብር በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለአንድ ወር በአካል ብቃት በስነ-ልቦና ግንባታና በሀገራዊ ፍቅር ላይ ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው።

በዚህም ሰልጣኞቹ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዠ ለኤር ሎጁስቲክ ብርጋዲየር ጀኔራል ነገራ ሌሊሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት ስልጠናው ባለሙያዎቹ የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በሚሰማሩበት የሙያ መስክ በስነ-ምግባርና በሀገር ፍቅር እንዲታነጹ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰው ሀብት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘነበወርቅ ገብረ ፃዲቅ በሁለቱ ተቋማት ትብብር የተሰጠ ስልጠና መሆኑን ጠቅሰዋል።

ስልጠናው አየር መንገዱ በሀገር ፍቅር፣ በስነ-ምግባር እና በአካል ብቃት የዳበረ የሰው ሀይልን ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ዕውን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ተመራቂዎች በበኩላቸው ስልጠናው አቅማቸውን በማዳበር ሀገራቸውን በቁርጠኝነት ለማገልገል መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።

በምረቃው በተጓዳኝም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ አንደኛ እና ሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች የትክሻ ምልክት የማልበስ ስነ ስርዓት መከናወኑን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም