የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም አስቸኳይ ስብሰባ በካምፓላ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም አስቸኳይ ስብሰባ በካምፓላ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ):- የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄድ ጀምሯል።
በስብሰባው መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እና ሌሎች የህብረቱ አመራሮች፣ የዩጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢና ናባንጃ፣ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው በስብሰባው እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በስብሰባው የካዴፕ የ10 ዓመት (ከእ.አ.አ 2015-25) የነበረው አፈጻጸም እንደሚገመገም ተገልጿል።
ዘላቂ የምግብ ምርታማነት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ የዜጎች ተጠቃሚነት፣ የማይበገር የምግብ ስርዓትን ግንባታ እና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ውይይት ከሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።
ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2035 የሚተገበረው የካዴፕ የ10 ዓመት ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚጸድቅም ይጠበቃል።
አስቸኳይ ስብሰባው እስከ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) የአጀንዳ 2063 አህጉራዊ ማዕቀፍ ነው።
ማዕቀፉ 23ኛው የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ በ2014 በኢኳቶሪያ ጊኒ ማላቦ ባካሄደው 23ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ የፀጸቀ ሲሆን ስያሜው የማላቦ ድንጋጌ (Malabo Declaration on Accelerated Agricultural Growth) እየተባለ ይጠራል።
ካዴፕ የአፍሪካ ሀገራት በግብርና መር ልማት ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ረሃብን እንዲያስወግዱ እና ድህነትን እንዲቀንሱ ማድረግን ዋነኛ አላማው አድርጓል።
በካዴፕ አማካኝነት የአፍሪካ መንግስታት ከዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው (ዲጂፒ) ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆነውን ለግብርና እና ገጠር ልማት ለመመደብ ተስማምተዋል።
በዚህም ሀገራቱ የግብርና ዘርፉን በየዓመቱ ቢያንስ በስድስት በመቶ ለማሳደግ አቅደው በመስራት ላይ ይገኛሉ።