የ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል።
የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ነው።
መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በአምስቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። አራት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ቡድኑ በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ድል ያላስመዘገበ ብቸኛው ክለብ ነው።
በሌላኛው የ13ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ ሰባት ግቦችን አስተናግዷል። አዳማ ከተማ በ15 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ድል ሲጎናጸፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ነጥብ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ 9ኛ ደረጃን ይዟል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ሲረታ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።