ኪነ-ጥበባዊ እሴቶችን በመጠቀም ገዢ ትርክትንና ብሔራዊነትን ለማስረጽ እየተሰራ ነው - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኪነ-ጥበባዊ እሴቶችን በመጠቀም ገዢ ትርክትንና ብሔራዊነትን ለማስረጽ እየተሰራ ነው - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2017(ኢዜአ)፡- በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ኪነ-ጥበባዊ እሴቶችን በመጠቀም ገዢ ትርክትንና ብሔራዊነትን ይበልጥ ለማስረጽ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያሏት፣ ታሪካዊ፣ የባለ-ብዙ ቅርሶች፣ ባህሎችና የተፈጥሮ ሃብቶች ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ትውልድ የሚኮራባቸውን አሻራ ያኖሩ ድንቅ ህዝቦች ናቸው፡፡
ለአብነትም የአድዋ ድል፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎሉ በርካታ የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በእነዚህና ሌሎች የጋራ መግባባትን በፈጠሩ ሀገራዊ ሁኑቶች ላይ ባህላዊ እሴቶችና ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገርን የሚያስተዋውቁ፣ በዜጎች መካከል አብሮነትንና ሰላምን የሚሰብኩ ባህላዊ እሴቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጉልህ ድርሻ አላቸው።
በተጨማሪም የሀገር ፍቅርን የሚሰብኩ፣ ታሪክን ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የሚያግዙ፣ አንድነትን የሚያጸኑ የኪነ-ጥበብ ስራዎችንም አንስተዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ባህላዊና ኪነ-ጥበባዊ እሴቶች ገዢ ትርክትንና ብሔራዊነትን ይበልጥ ማስረጽ እንዲችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
ለአብነትም ለሶስት ወር ሲካሔድ የቆየው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ንቅናቄ አንዱ መሆኑን ጠቁመው ንቅናቄው የዜጎችን አብሮነት የሚሰብኩ፣ የሀገር ገጽታን የሚገነቡና የሚያስተዋውቁ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ማጉላቱንም ጠቁመዋል፡፡
ንቅናቄው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በስራዎቻቸው የህዝቦችን አንድነት ሰላምና፣ የሀገርን ገጽታ የሚገነቡ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ለሌሎች መነሳሳትን እንዲፈጥር ታልሞ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የምስራቅ አፍሪካ የባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫልን ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ስራ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ብሎም ለትውልዱ ከጥላቻ የጸዳች ሀገር የማስረከብ ስራ መሆኑን መረዳትና ለስኬታማነቱ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በተለይም ከኪነ-ጥበብ ባለሙያው ጋር በቅርበት መስራትና በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ የሚከናወኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።