በኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸው አበርክቶ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸው አበርክቶ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 30/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸው አበርክቶ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ታሪክ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ሌሎችም ማህበራዊ መሰረት ያላቸው የግጭት መፍቻ ስልቶች የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብቱ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል።
ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ጠንካራ ማህበራዊ መሰረት ያላቸው ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን ማህበራዊ ተቋማት የማህበረሰቡን ቱባ ባህልና እሴት ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ገንቢ ሀገራዊ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
በየዘመኑ የነበሩ መንግሥታት ችግር ሲገጥማቸው ሀገርን በማረጋጋት እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ ተቋማት መሆናቸውንም አውስተዋል።
በመሆኑም ችግሮች እንዳይፈጠሩ በማስተማር፣ ሲፈጠሩ በማረጋጋት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የነበራቸው ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ከ75 በላይ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች እንዳሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸው አበርክቶ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚኖሩባት ሰላማዊና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ገለልተኝነታቸውንና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የብዝኃ ሃይማኖት መገኛ እንደመሆኗ የእምነት ተቋማቱ ግጭት እንዳይከሰት የማስተማርና ሲከሰትም በቀላሉ በምክክር እንዲፈታ የሚያደርጉትን አወንታዊ ሚና ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
መንግሥት ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን በማዳበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡