ቀጥታ፡

የሊጉ 13ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 30/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።  

የመጀመሪያው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ እና ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።  ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታቹ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል።

 ቡድኑ በ10 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።  

ተጋጣሚው  ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።  

በአምስት ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ሁለት ግቦች ተቆጥረውበታል።

ባህር ዳር ከተማ በ19 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።   በ13ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።  ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ አምስት ጎሎችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።   ድሬዳዋ በ17 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።   በአምስቱ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ15 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።    

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል መቀሌ 70 እንደርታ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።  

አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የ13ኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።  

የ13ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።   ሀዲያ ሆሳዕና ሊጉን በ22 ነጥብ ሲመራ ፣ መቻል በ21 ነጥብ ይከተላል።

የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር እና የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ በስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመሩ ነው።

ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ፣ የመቻሉ ሽመልስ በቀለ፣ የአዳማ ከተማው ነቢል ኑሪ እና የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም