የካፒታል ገበያ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል- ሀና ተኸልቁ - ኢዜአ አማርኛ
የካፒታል ገበያ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል- ሀና ተኸልቁ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 29/2017(ኢዜአ):- የካፒታል ገበያ የፋይናንስ አካታችነት ለማረጋገጥ እና ለኢኮኖሚያዊ ማሻሻያው ትግበራ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሯ ይህ ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ነው።
ካፒታል ገበያ የፋይናንስ አካታችነት፣ ለሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ውጤታማነት፣ ዘላቂነት ያለው የፋይናንስ አማራጭ ለመፍጠርና የሀብት ምንጮችን ለማስፋት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የመንግስታት ለውጥ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ና ማህበራዊ ሁኔታዎች፣ የግሉ ዘርፍ የነበረው የተዛባ አተያይ፣ የቴክኖሎጂ ውስንነት እና መሰል ምክንያቶች ካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ለማቋቋም እንዳላስቻሉ እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ከኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤቶች አንዱ የካፒታል ገበያ መቋቋም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ይህም ለግሉ ዘርፍ መጠናከርና ለማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ጠንካራ የካፒታል ገበያ ስርዓት ለመገንባት ደግሞ ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካል፣ ተአማኒ የገበያ አገናኝ፣ ቴክኖሎጂ፣ አስቻይ ማዕቀፍና ዘርፉን በብዝሃ የአክሲዮን ባለቤትነት የሚመራ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።
በዚህም መንግስት የካፒታል ገበያ ሲፈቅድ አስቻይ የሕግ ማዕቀፍና ዘርፉን የሚመራውን የካፒታል ገበያ ባለስልጣን እንዲቋቋም ማድረጉን አውስተዋል።
ባለስልጣኑም በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በመንግስትና በግል ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት ለተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተለያዩ ሰነደ ሙዓለነዋዮችን ያገበያይ ዘንድ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ተቋማዊ የመፈጸም አቋሙን ለመገንባትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት አስቻይ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በካፒታል ገበያ ስርዓቱ አሰራሮች የሚመሩበትና ጥፋቶች የሚዳኙበት የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
በዘርፉ ለሚሰማሩ ዓለም አቀፍ ተዋንያን በግልም ሆነ በሽርክና የሚሰማሩበት አሰራር የማመቻቸት፣ ፈቃድ የመስጠትና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም እንዲሁ።
ካፒታል ገበያ መንግስት በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለማከናወን ቃል የገባቸውን ተግባራት በቀጣይነትና ጥሩ ሁኔታ እየፈጸመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።