ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት በርዕደ መሬት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን እየደገፈ ነው- ሙሳ አደም(ዶ/ር)

ሠመራ፤ ታኅሣሥ 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአፋር ክልል በርዕደ መሬት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አደጋው በደረሰበት የገቢ ረሱ ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባል ሙሳ አደም(ዶ/ር) ገለጹ።

ሰራዊቱ በአዋሽ ፈንታሌና በዱለሳ ወረዳዎች በርዕደ መሬት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ከአደጋ ቀጣና በማውጣት ሕይወት አድን ስራ እየሰራ ነው ተብሏል።

በክልሉ ገቢ ረሱ ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባልና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙሳ አደም(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በችግር ቀን ደራሽ መሆኑን ያሳየበትን ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ገልጸዋል።

የሰላም ዘብ የሆነው ሰራዊቱ ለርዕደ መሬቱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን በ14 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በማጓጓዝ ህይወት የመታደግ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ከአደጋ ቀጣና ከማንቀሳቀስ ባሻገር የመጠጥ ውሃ እና ሌሎች ድጋፎችን በማቅረብ አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሰራዊቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የአደጋ ስጋት ካለባቸው ቦታዎች የማንሳት ተግባሩን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ሰራዊቱ ስፍራው የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሚገኝበት በመሆኑ የፋብሪካውን ደህንነትና የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ረገድም ግዳጁን እየተወጣ ነውም ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የህዝብ አጋርነቱን በተለያዩ ተግባራት ማስመስከር መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም