የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 29/2017(ኢዜአ):- ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች፣ አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት(ገና) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ለእምነቱ ተከታዮች መልካም ምኞቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የገና በዓል እንዲሆን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ቁርኝት ያለው መሆኑን በማንሳት ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ትስስር ጭምር እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም ቱሪዝም ለሁለቱም ሀገሮች የምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግና የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር በትብብር እንሰራለን ሲሉ ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር አብዲ መሀመድ እይቤ ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቼ እንኳን ለገና በዓል አደረሳችሁ ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
በዓሉ የሰላም እና የደስታ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት(ገና) በዓል አደረሳችሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ምክትል የልማት ዳይሬክተር ቪሴንቴ ሶሌራ-ዱካር ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልካም ገናን እመኛለሁ።
በዓሉ የፍቅር፣ የጤና እና የሰላም ይሁን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን የደስታ ወቅት በሆነው የገና በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወንድሞችና እህቶቼ መልካም በዓል እንዲሆን ልባዊ ምኞቴ ነው ብለዋል።
በዓሉ አንድነትን፣ ብልጽግናና ደስታን ይዞ እንዲመጣም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ካናዳ ለኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓል የደስታ እንዲሆን ምኞቷን ትገልጻለች ሲል አመልክቷል።
ይህ የበዓል ወቅት ለእምነቱ ተከታዮች ደስታ እና ስፍር ቁጥር የሌለው በረከት ይዞ እንዲመጣም ተመኝቷል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ፣ የቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ የስዊድን፣ የስፔን፣ የሜክሲኮ እና የስሪላንካ ኤምባሲዎች ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም የገና በአል ይሁንላችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተያያዘም የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ኤጀንሲ(ዩኤን ውመን)፣ ሴቭ ዘ ችልድረን እና ወርልድ ቪዥን ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ በማድረግ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ይገኙበታል።