ቀጥታ፡

አመራሩ በተለወጠ የስራ ባህል የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነቱን በማጠናከር የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል አለበት- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ ፤ታኅሣሥ 28/2017(ኢዜአ):- አመራሩ በተለወጠ የስራ ባህል የተግባር እና የአስተሳሰብ አንድነቱን በማጠናከር የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የሐረሪ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የቅድመ ፓርቲ ውይይት ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ ለህዝብ ቃል የገባውን በመተግበር ረገድ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል።


 

ለዚህም ፓርቲው ባካሄደው የአንደኛው መደበኛ ጉባኤ ለህዝብ በገባው ቃል መሠረት ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ስራዎች በቁርጠኝነት ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

በክልሉ በተለይም ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ስራዎች እውን ማድረግ መቻሉን አንተዋል።


 

በክልሉ ከስራ ባህልና ሰዓት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ተጨባጭ መሻሻሎች እንደታዩ በመግለፅ በቀጣይም በስራ ባህል ላይ እየታየ ለውጥ በማጠናከርና ባህል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የተግባር እና የአስተሳሰብ አንድነቱን በማጠናከር እንደ ክልል የተመዘገቡ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ማላቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም በኢኮኖሚ፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ሌሎች የልማት መስኮች የተገኙ ውጤቶችን ማጎልበት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በአፈጻጸም ረገድ ያሉ ውስንነቶች በመገምገም የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አሁንም የላቀ ትኩረት መስጠትና ህዝቡ የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመው የአመራሩ አንዱ መመዘኛም ለህዝቡ በሰጠው አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋማትን በአሰራር፣ በአደረጃጀት እና በሰው ኃይል ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል።

አመራሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣትና ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ፣የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሪፍ መሀመድን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ መንግሥት እና የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም