በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ለኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ለኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 28/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ለኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
የኢትዮጵያና እስራኤል ጠንካራና ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከሩንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር)፤ ከበዓሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ ጥልቅ እሴቶች ያሉት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፥ በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅርና መተሳሰብ እሴቶችን የሰነቀ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመሆኑም ይህንኑ በዓል ለሚያከብሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው በመመኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ቁርኝት ያለው መሆኑን በማንሳት ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ትስስር ጭምር እንዳላቸው አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያን በእስራኤል የሚገኙ ቅዱስ ስፍራዎችን በመጎብኘት እንደሚታወቁም ጠቅሰዋል።
ለሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጠናከር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወሳኝ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
በቀጣይም ቱሪዝም ለሁለቱም አገሮች የምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግና የአገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያና እስራኤል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን በተለይም በጤና፣ ኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።