ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ታኅሣሥ 28/2017 (ኢዜአ):- የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የከንቲባዋ የበዓል መልዕክት ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
እየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጆች እና በአምላክ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ በምህረት፣ በይቅርታ እና በታላቅ ፍቅር ወደ ምድር መምጣቱ ሰላምን እና ፍቅርን ለምድር እንዲሁም አብሮነት እንዲጎለብት ምሳሌ ለመሆን ነው።
ስለዚህ በዓሉን ስናከብር የእየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነትን በመከተል የሰላም እሴቶችን እየገነባን፣ ፍቅራችንን ይበልጥ እያጎለበትን እንዲሁም አብሮነታችንን እያጠናከርን ሊሆን ይገባል።
በዓሉን ስናከብር ያላቸው ለሌላቸው ማዕድ በማጋራት ፍቅር፣ መተሳሰብና አብሮነት በሚገለጽበት መልክ እንዲሆን ጥሪ እያቀረብኩ፣ የሰላም እና የደስታ በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።