ቀጥታ፡

የገና በዓልን ስናከብር ካለን ላይ ለሌላው ማካፈል ይጠበቅብናል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2017(ኢዜአ)፡- የገና በዓልን ስናከብር ካለን ላይ ለሌላው ማካፈል  እንደሚጠበቅብን የእምነት አባቶች ተናገሩ፡፡

በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

ሰዎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ስጦታ የመለዋወጥ የቆየ ባህል ያላቸው ሲሆን ይህ ደግሞ የፍቅር መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የገና በዓልና ስጦታን በተመለከተ ኢዜአ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቆሞስ እና የኢትዮጵያ ካህናት ማህበር ሰብሳቢ ከሆኑት ከአባ ፍሰሃ ታፈሰ ጋር ቆይታ አድርጓል። 

"ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለእኛ ስጦታ ነው" ያሉት አባ ታፈሰ፤ ገና ሲመጣ ይሄን ስጦታ የምናድስበት ነው ይላሉ።

ስጦታ ሰው ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ራሱን ለማረም በጌታ ብርታት ትክክለኛውን መንገድ ለመጓዝ እንዲችል ትልቅ በረከት የሚያገኝበት መሆኑንም ይገልጻሉ።

የገና በዓልን ስናከብር ካለን ላይ ለሌላው ማካፈል ይጠበቅብናል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። 

በስጦታ መልክ የሚሰጠው ነገር የብዛትና የመጠን ሳይሆን ካለን ላይ በደስታና በፍቅር ለምንሰጠው ሰው የደስታ ምንጭ መሆን ነው ይላሉ።

በዚህም በችግር ላይ ለሚገኝ ጎረቤታችን ካለን ላይ ማካፈል እንዳለብን በማሳሰብ ለዚህም ከራስ ወዳድነት በመውጣት ወደ ሌላው መሻገር አለብን ሲሉም ጠቁመዋል።

"ህይወታችንን፣ ጊዜያችንንና ገንዘባችንን በመስጠትና በፍቅር በመለገስ ብዙ በረከቶችን እናገኛለን" ብለዋል።

ከቁሳዊ ስጦታ በፊት ሰዎች እርስ በርሳቸው አንዱ ለአንዱ ፍቅር እና ምህረትን መስጠት አለበት በማለት አሳስበዋል።

ከራሳችን አሳልፈን ለተቸገሩ መስጠት፣ በፍቅር ለመኖር፣ የበደሉንን ይቅር ለማለት እና ያለፈን ትተን በፍቅር መረማመድ አለብን ብለዋል።

"ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያ የተሰጠው ዝማሬ ነው" እረኞች የሚሰጡት ስጦታ ስላልነበራቸው የሰጡት ነገር ዝማሬ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ይህም የምንሰጠው ምስጋና ራሱ ትልቅ ቦታ እንዳለው ያሳያል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሰውን መጠየቅ ከማንኛውም ስጦታ በላይ መሆኑን አንስተው ፍቅር ማስቀደም አለብን ይላሉ። 

የስጦታ መጀመሪያ ስነ-ምግባር ሁለተኛው ደግሞ ካለን ላይ ማካፈል መሆኑን በመጥቀስ ሁሉም ሰው ባለው አቅም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአቅሙን ማድረግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ከራሳችን አልፈን ሌሎችን መርዳት፣ ለጋስና ቸር በመሆን በፍቅር መስጠት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የታረዙትን በማልበስ እና የተራቡትን በማብላት የገና በዓልን ልናሳልፍ ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሓፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው።   

"ፈጣሪ ለሰው ልጆች አንድ ልጁን በስጦታ ሰጥቶናል" በዚህ ምሳሌ እኛም ካለን ላይ ሌሎች ማካፈል አለብን ብለዋል።

"ስጦታ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል፤ለእኛም ትልቅ የውስጥ እርካታ ይሰጣል" በመሆኑም በዓልን በዚህ መልክ ልናሳልፍ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ፈጣሪ ልጁን በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ ለእኛ ሰጥቶናል፣እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ፍቅር በመለዋወጥ ሰላምን አብዝተን ልንሰብክ ይገባል ብለዋል። 

ስጦታ ሰዎች እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅርና ሰላም እንደሚያበዛና የተሳሳተ እይታቸውን ቀና እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዓሉን ስናከብር ካለን ላይ ለሌሎች በማካፈል መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

እግዚአብሔር ለእኛ ከሰጠን ላይ አንስተን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ማገዝ የህሊና እርካታና ሰላም ይሰጣል ብለዋል ።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም