ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ከሚፈፀም ማጭበርበር ራሱን መጠበቅ አለበት - የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 28/2017(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ከሚፈፀም ማጭበርበር ራሱን መጠበቅ እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።

ፖሊስ የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወይም ገና አንዱ ነው።

በዓሉ ከኃይማኖታዊ ስርዓት ባሻገር በተለያዩ ሁኔታዎች የሚከበር ሲሆን ማህበረሰቡ ከዋዜማ ጀምሮ የበዓል ግብይትን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅት ያደርጋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት የፀጥታ ግብረ ኃይል የገና በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ  ወደ ስራ ገብቷል።

በቅድመ ዝግጅቱ በዓልን መሰረት አድርገው ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየት መከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በበዓል ሰሞን የማታለል፣ የማጭበርበር፣ ቅሚያ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ግብይት መፈፀም፣ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ መሸጥ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በመዝናኛ ቦታዎች ላይ ፀብ እንዲሁም መሰል የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ የፀጥታው ኃይል አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

ፖሊስ መደበኛ እና የባዛር ግብይት ባለባቸው አካባቢዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ወንጀልን የመከላከል ስራ እያከናወነ  እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የህዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ በመዝናኛና ሌሎች ስፍራዎችም በጥንቃቄ መንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠጥቶ ማሽከርከር የበዓላት ወቅት ዋነኛ የትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆኑንም ጠቁመው ፤ይህን ለመከላከል ቀንና ማታ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአልኮል ቴስተር ምርመራ በስፋት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ፖሊስ የሚያስተላልፈውን የጥንቃቄ መልዕክት በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በአቅራቢያው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በግንባር በመቅረብ ወይም በስልክ ቁጥሮች 011-1-11-01-11 እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም