ተቋሙ ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል_ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል_ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28/2017(ኢዜአ)፦ አየር ኃይል ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዡ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።
አየር ኃይሉ እያከናወናቸው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የስራ እና የግዳጅ አፈፃፀም እንቅስቃሴዎች ውጤታማ መሆናቸውን ዋና አዛዡ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በየዘመናቱ ሁሉ የተሰጡትን ሃገራዊ ግዳጅ እና ተልዕኮዎችን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ዛሬ ላይ የደረሰ በድል እና በመስዋዕትነት የደመቀ አኩሪ ታሪክ ያለው አንጋፋና ስመ ገናና የአቪዬሽን ተቋም ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ አሁንም ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራጅቶ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በንቃት እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ዘመናዊ የስልጠና ሂደትን በመከተል ብቃት ያላቸው ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትኩረቱን የአየር ኃይል አካዳሚ ላይ በማድረግ የዘመኑን የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን ገልፀዋል።
"ለታላቅ ሃገር ታላቅ አየር ኃይል" በሚል መርህ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ተቋም ለመገንባት እንዲቻል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በውጊያ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅ እና በማሻሻል እንዲሁም ምቹ እና ፅዱ የስራ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ባከናወናቸው ዙሪያ መለስ የለውጥ ስራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ዋና አዛዡ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የአቪዬሽን ተቋም ለማድረግ የተያዝነው ራዕይ በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ መሆኑን ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአሁኑ ወቅትም ሀገራችንን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የጥፋት ቡድኖች ለመከላከል በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።