ጉባዔው ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት(ገና) በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ።
ጉባዔው የ2017 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ክብረ በዓልን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል ተመኝቷል።
ጉባዔው በመግለጫው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የደህነታችን ተስፋ ዕውን እንደሚሆን የተበሠረበት፣ ለሠው ልጆች የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ፣ በሀጢያት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ እና ርቆ ለነበረው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር የመመለሡ ተስፋ የተረጋገጠበት ታላቅ የድል ብስራት ጅምር ነው ብሏል፡፡
ብርሃነ ልደቱ ከእግዚአብሄር ርቀው ለነበሩ ሕዝቦች ወደ ፈጣሪ የመመለሻ ደወል የተደወለበት፣ ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ተስፋ እርግጠኝነት የተበሠረበት፣ መለያየት በዕርቅ የሚተካበት ጊዜ እንደተቃረበ በተግባር የተረጋገጠበት ታላቅ ክብረ በዓል እንደሆነም ገልጿል።
በብርሃነ ልደቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን፣ መሰጠትን፣ አገልጋይነትን፣ ፍቅርን እና የርህራሄ አስተምህሮዎችን በተግባር ያሳየበት ክስተት እንደሆነ ጠቁሟል።
በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ለሀገርና ለህዝብ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመፀለይ፣ የተቸገሩትን በመርዳት እና በመደገፍ፣ በሕመም አልጋ ላይ የሚገኙትን ወገኖቻችንን በመጠየቅ፣ በማበረታታት እና በመርዳት፣ በሕግ ጥላስር በመሆን በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙትን የሕግ ታራሚ ወገኖቻችንን በመጎብኝት መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርቧል፡፡