ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተገነቡ ቤቶችን ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተገነቡ ቤቶችን ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2017(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተገነቡ ቤቶችን ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የገነባናቸው ቤቶች እና የስራ እድል ለተፈጠረላቸው የልማት ተነሺ የከተማችን ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታዎችን አስተላልፈን እንኳን አደረሳችሁ ብለን ማዕድ አጋርተናል ብለዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብቻ በኮሪደር ልማትና በመንገድ ወሰን ማስከበር ለተነሱ 4ሺህ 510 እማወራ እና አባወራዎች ንጹህ እና መሠረተ ልማት የተሟሉላቸው መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተን ያስተላለፍን ሲሆን 1264 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ የስራ እድል ፈጥረን የመስሪያ ቦታዎችን አስረክበናል ሲሉም ገልጸዋል።
አዳዲስ 4 ህንጻዎች በአያት ሪል ስቴት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ጄ ኤፍ ኤም ፔትሮሊየም ዲስትሪቢዩሽን እንዲሁም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሲሆን በተጨማሪም በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአቃቂ ቃሊቲ 48 ቤቶችን እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ 141 ቤቶችን ገንብተን ለነዋሪዎች አስተላልፈናል ነው ያሉት።
ከንቲባዋ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ባለሃብቶችን በነዋሪዎቹ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።