ለገና በዓል የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል - ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
ለገና በዓል የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት ተደርጓል - ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2017(ኢዜአ)፡- በነገው ዕለት ለሚከበረው የገና በዓል የኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ።
የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሚኪያስ ወንድሙ የገና በዓል የኃይል አጠቃቀም ከሌሎች በዓላት የኃይል ጭነቱ ከፍ የማለት አዝማሚያ ስለሚስተዋል ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በበዓሉ ወቅት የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ካለፉት ዓመታት የበዓል የኃይል አጠቃቀም አዝማሚያ በመነሳት 4 ሺህ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ዝግጁ መደረጉን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በበዓሉ ዕለት የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም ለማድረግ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሁሉም ዩኒቶች ላይ የፍተሻ ሥራዎችን በማከናወን ዩኒቶቹ ዝግጁ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለኃይል መቋረጥ ምክንያት እንዳይሆኑ የቅድመ መከላከልና የፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውንም አስረድተዋል።
በበዓሉ ምክንያት ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች እና ለጎረቤት አገራት በሚቀርበው ኃይል ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖር መጠቆማቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለማህበረሰቡ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ሲባል ከ11 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል የሚያገኙ የአገልግሎቱ የኢንዱስትሪ ደንበኞች በበዓሉ ወቅት አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ንግግር መደረጉንም አንስተዋል።