ርዕደ መሬትና እሳተ ጎመራ፤ ተሞክሮዎችና ጥንቃቄዎቹ!

ከዓለማችን ተፈጥራዊ አደጋዎች መካከል ይጠቀሳሉ-ርዕደ መሬትና የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ። የመሬት መንቀጥቀጥ (ርዕደ መሬት) የመሬት ስር ዓለቶች ግጭት ውጤት ነው። በሳይንስ መሬት ቅርፊት (Crust)፣ መካከለኛ ንጣፍ(Mantle) እና አስኳል(core) በሚሰኙ ንብርብሮች የተዋቀራች ናት። የቅርፊቱ(የላይኛው አካለ-መሬት) እና የማንትል (የመካከለኛው አካለ-መሬት) ያስተሳሰረው ክፍል ሊቶስፌር (lithosphere) ይሰኛል። ይህ መገጣጠሚያ ስፍራ ሁልጊዜም በማያቋርጥ ሜካኒካዊ እንቅስቃሴ ላይ ነው። ይህ እረፍት አልባ ውስጣዊ መናወጥ ታዲያ በሂደት መሬትን ያንቀጠቅጣል። ርዕደ መሬት ይፈጥራል ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት ርዕደ መሬት መከሰቱ ዕሙን ነው። ከአንድ ወር ወዲህ የጀመረው የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የተነሳው የመሬት መንቀጥቀጥ ድግግሞሽ ከሰሞኑ ተባብሶ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት መረጃ እንዳመለከተው ከሰሞኑ ከፍተኛ የተባለ(በርዕደ መሬት ልኬት 5 ነጥብ 8) መሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። ንዝረቱም በአዲስ አባባና በሌሎች ከተሞች ተሰምቷል።

ኢትዮጵያ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካል በመሆኗ የመሬት መንቀጥቀጥ በየጊዜው ያጥማታል። በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት መረጃ መሰረት በ1900 ዓ.ም 6 ነጥብ 7፣ በ1909 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 እንዲሁም በ1961 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ያውቃል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ ለኢዜአ እንዳሉት በአፋር ክልል በአዋሽ ፈንታሌ በተሰኘው የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በ2016 ዓ.ም መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት እንደነበር ያስታውሳሉ። በቅርቡ የተከሰተው የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ርዕደ መሬትም ከቅልጥ ዓለት ጋር የተያያዘ ነው። በአዋሽ ፈንታሌ ሳቡሬ አካባቢ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጡ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል በመጠቆም ቅልጥ ዐለቱ ባለበት እንደሚረጋጋ ካልሆነም የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ኤልያስ ሌዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ ያለው በመሬት ውስጥ ያለው የማግማ( ቅልጥ አለት) እንቅስቃሴ ኃይል ባለመቆሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ኃይለኛ እሳተ ገሞራ መኖሩን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በእሳተ-ገሞራና በአለቶች ግጭት ይፈጠራሉ። ፕሮፌሰር አታላይ እንደሚሉት መሬት ሁልጊዜም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ እሳተ ገሞራ፣ መሬት መንሸራተትና መንቀጥቀጥና መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጠባቂ ክስተቶች እንደሆኑም ያነሳሉ።

” አሁን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ማብቃቱ አይቀርም፤ ነገር ግን መች እንደሚያበቃ ማወቅ አይቻልም ” – አታላይ አየለ (ፕ/ር)

ሰሞነኛ የአፋር ክልል ዱላቻ ወረዳ ዳፋን ተራራ ላይ የታመቀ ውሃ እና እንፋሎት መከሰቱን የኢትዮጵያ ጆኦሎጂካል ኢኒስቲትዩት መረጃ ያሳያል። ክስተቱ በአካባቢ ከነበረው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አኳያ የሚጠበቅ መሆኑንም ገልጿል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት 5 ነጥብ 0 እስከ 5 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የሚመዘገብ  የመሬት መንቀጥቀጥ መጠነኛ የሚባልና በደንብ ባልተገነቡ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ነው። 7 ነጥብ 0 ነጥብ 7 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የመሬት መንቀጥቀጥ መሠረተ ልማት እና ሕንፃዎች ሊያፈርስ ይችላል። በሌላ በኩል በሬክተር ስኬል ከ8 ነጥብ 0 እና ከዚያ በላይ ከሆነ ክስተቱ የሰው ህይወት ማጥፋትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ውድመት ያስከትላል።            

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰዎች የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ሊያደርሱ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ሰው ሰራሽ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች “induced earthquakes” ተብለው ይጠራሉ።

የማዕድን ቁፋሮ፣ የተበከለ ውሃ፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድና ሌሎች ፈሳሾችን በከፍተኛ ጫና ወደ መሬት መልቀቅ፤ በነዳጅ ማውጣት ወቅት የተበከለ ውሃን ጥቅም ላይ ማዋል፣ ፈሳሽን በከፍተኛ ጫና ወደ መሬት ውስጣዊ ክፍል በመልቀቅና መሰል ሰው ሰራሽ ምክንያቶች መሬት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥም ይችላል። ለአብነትም በአውሮፓዊያኑ 2008 በቻይና ሲሹዋን ግዛት በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 9 የተመዘገበውና 87 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ህይወትን የቀጠፈው ርዕደ መሬት በሰው ሰራሽ ምክንያት የተከሰተ በሚል ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ የሚባል ርዕደ መሬት አጋጥሞ አያውቅም። በዓለማችን ግን ለመልከ ብዙ ቀውስ የዳረጉ አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በተለያዩ ዘመናት ተከስተዋል።

አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1960 በሀገረ-ቺሊ በሬክተር ስኬል 9 ነጥብ 5 የተመዘገበው ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት 1 ሺህ 665 ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። ለሱናሚ (ለውቅያኖስ አውሎ ነፋስ) መሰከትም መንስኤ ሆኗል።

1964 በአሜሪካ አላስካ ግዛት በተከሰተውና 9 ነጥብ 2 ሬክተር ስኬል የተመዘገገበት አደጋ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ንብረት አውድሟል። በርዕደ መሬቱ በተነሳው ሱናሚም 122 ሰዎች ሞተዋል።

በ2004 በህንድ ውቅያኖስ በተከሰተው የ9 ነጥብ 2 ሬክተር ስኬል መሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በ17 ሀገራትን ያካለለ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን የ227 ሺህ 898 ዜጎች ህይወት አልፏል። በታይላንድ ብቻ 3 ሺህ 950 ሰዎች በዚሁ ወቅት ሞተዋል።

በ1920 በቻይና ሃይዩዋን አካባቢ በሬክተር ስኬል 8 ነጥብ 5 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ73 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል። በ1976 በቻይና ታንግሻን ከተማ 7 ነጥብ 6 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ 242 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። 700 ሺህ ሰዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። 10 ቢሊዮን ዶላር ንብረት ወድሟል።

                              

                   የጥንቃቄ እርምጃዎች እና የመንግስት ጥረት

ሰሞነኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ድግግሞሸን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደሚገባ አመልክቷል።

በዚህም ከቤት ውጭ ከሆኑ፦ ከዛፎች፣ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌትሪክ ምሶሶዎች እና ሌሎች ወድቀው ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ እና ገላጣ ሜዳ አካባቢ መቆየት።

በቤት ውስጥ ከሆኑ በበር መቃኖች፣ ኮርነሮች እና ኮሪደሮች ተጠግቶ ማሳለፍ። ከእሳት ምድጃዎች፣ ከተሰቀሉ ፍሬሞች እና የግድግዳ ጌጦች፣ ከመጽሐፍ መደርደሪያዎች እንዲሁም ከመስኮት አካባቢ መራቅ። የጋዝ ምድጃዎችን በተቻለ ፍጥነት ማጥፋት ካልሆነም ከአካባቢው መራቅ።

በትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥ ከሆኑ፦ ከሕንጻዎቹ ለመውጣት አለመሞከር አሳንሰር (ሊፍት) በፍፁም አለመጠቀም። ከደረጃዎች አካባቢ መራቅ።

መኪና እያሽከረከሩ ከሆኑ፦ የኤሌትሪክ መተላለፊያ ምሶሶዎችን፣ ዛፎችና ሽቦዎች አካባቢ አለመቆም፣ የኤሌትሪክ መስመር ምሶሶዎች እና ሽቦዎች ተሽርካሪው ላይ ከወደቁ ከመኪናው ለመውጣት አለመሞከር፣ በተቻለ ፍጥነት ገላጣ ወደሆነ አካባቢ መኪናን ማቆም እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

በተመሳሳይ የአጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም የጥንቃቄ እርምጃዎችንና ተያያዥ የድጋፍ ዝግጁነት ተግባራቱን አሳውቋል። በዚህም በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ(ዱለሳ) ወረዳዎች ውስጥ በፈንታሌ ወረዳ 15,000 ነዋሪዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ጨቅሶ፤ እስከ አሁን 7,000 ወገኖች ከስጋቱ ቀጠና ወደ ሌላ ስፈራ መጓጓዛቸውን ገልጿል። በዱለቻ ወረዳ ደግሞ 20,000 የሚሆኑ 2 ቀበሌዎች ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ቀበሌዎች እስከ አሁን 6,223 ህዝብ አካባቢውን ለቀዋል፡፡  በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ 5 ቀበሌዎች ወገኖች ለአደጋው ተጋላጭ ናቸው፡፡ 5ቱም ቀበሌዎች 16,182 ሕዝብ ተጋላጭ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 7,350 ሕዝብ ከተጋላጭ ስፍራ ወጥተዋል፡፡ 8,832 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ እስከ አሁን 70,000 የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን 11,550 ኩንታል ምግብ-ነክ እና 7,000 አባወራ የሚሆን ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው ተልኳል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን ለምግብ ብር 216,562,500.00 እና ምግብ-ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች ብር 65,625,000.00 በድምሩ ብር 281,562,500 (ሁለት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር) የሚገመት ነው፡፡ 

May be an image of text

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ርዕደ መሬት በታየባቸው አካባቢዎች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ታሳቢ ሁኔታዎች ላይ ምልከታ እያደረጉ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አገልግሎቱ በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያላቸው ርዕደ መሬቶች ክስተቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሷል። የዘርፉ ባለሙያዎች ክስተቶቹን በቅርብ እየተከታተሉ እንደሆነና በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት መንግስት በ12 ቀበሌዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ መረጃ እያሰባሰበ እንደሚገኝ ተገልጿል። በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች መካከል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማስፈር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል። ርዕደ መሬቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሳስቧል።

 

No photo description available.

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም