ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ የተመራ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ለድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ የተመራ የቻይና የጤና ባለሙያዎች ቡድን ለድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የጤና መገልገያ ቁሶችና መድኃኒቶች ድጋፍ አደረገ።

በአምባሳደሩ የተመራው ቡድን ዛሬ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ተገኝቶ ህሙማንን የጎበኘ ሲሆን፤ ለሆስፒታሉ የተለያዩ መድኃኒቶችና የጤና መገልገያ መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።


 

አምባሳደር ቼን በዚሁ ወቅት፤ ሪፈራል ሆስፒታሉ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል መሠረታዊ የጤና አገልግሎት አየሰጠ መሆኑን አይተናል ብለዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የድሬዳዋ ጣቢያን መጎብኘታቸውን የገለፁት አምባሳደሩ፤ ድሬዳዋ የኢትዮጵያ እና የአካባቢው የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከል መሆኗን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የቻይና ባለሃብቶች በከተማዋ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲያሳድጉ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለፁት።


 

ለአምባሳደሩ አቀባበል ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ኤምባሲው ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ የቻይና ባለሃብቶች በድሬዳዋ በተለያዩ የልማት ተግባራት መሰማራታቸውን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ይህ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የህክምና ቁሶች ድጋፍ የተደረገለት የድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር በረከት ገብሩ በበኩላቸው ኤምባሲው ያደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የቻይና የህክምና ባለሙያዎች ቡድን በሆስፒታሉ ተገኝቶ ለህክምና ባለሙያዎች የሰጠው የልምድና የዕውቀት ሽግግር ለቀጣይ ስራ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም