የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ተከትሎ በጊዜያዊ መጠለያ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ድጋፍ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ተከትሎ በጊዜያዊ መጠለያ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ድጋፍ እየቀረበ ነው
ሠመራ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- በአዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በጊዜያዊ መጠለያ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ክልሉ አስታወቀ።
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከስፍራው የማዛወር ስራ ተሰርቷል።
ነዋሪዎቹ በሰፈሩበት ቦታ የዕለት ምግብና ውሃ የማድረስ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን አደጋው በተከሰተበት ገቢ ራሱ ዞን አካባቢ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪና የክልሉ ወጣቶች ባህልና ሰፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም ተናግረዋል።
አቶ አህመድ ኢብራሂም በአዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉትን የማንቀሳቀስና የማዛወር ስራ ተከናውኗል።
ከትናንት ጀምሮ በአካባቢው በመገኘት አጠቃላይ ሁኔታዎችን በማጤን ለህብረተሰቡ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻል እና የከፋ ጉዳት እንዳያጋጥም እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከሁለቱ ወረዳዎች የተፈናቀሉት የአካባቢው ነዋሪዎች በአሚበራ ወረዳ ሲዳሃ ፋጌ ቀበሌ እንዲሰፍሩ መደረጉም ታውቋል።
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የርዕደ- መሬት ክስተት የተፈጥሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደውልን ተከተሎ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታና ምላሽ እየታየ ያለው ስራ አመርቂ ነው፡፡
በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች ማለትም አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ(ዱለሳ) ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በሁለቱም ወረዳዎች ማለትም በአዋሽ ፈንታሌ 6 ተጋላጭ ቀበሌዎች 15,000 ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ እስከ አሁን 7,000 ወገኖች ከስጋቱ ቀጠና ወደ ሌላ ስፈራ ተጓጉዘዋል፡፡
በዱለቻ ወረዳ ደግሞ 20,000 የሚሆኑ የ2 ቀበሌዎች ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ቀበሌዎች እስከ አሁን 6,223 ህዝብ አካባቢውን መልቀቃቸውን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡