በባዛሩ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ይዘው መቅረባቸውን - አምራቾች - ኢዜአ አማርኛ
በባዛሩ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ይዘው መቅረባቸውን - አምራቾች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- በባዛሩ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባዘጋጀው ባዛር የተሳተፉ አምራቾች ገለፁ።
በበዓላት የሚደረጉ ባዛሮች የገበያ መዳረሻቸውን የሚያሰፉና ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዛቸውም አምራቾቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከታህሳስ 18 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የ''እኛን ምርት ለእኛ" በሚል ባዘጋጀው ኤግዚብሽንና ባዛር አምራቾች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲሁም አልባሳትን ይዘው ቀርበዋል።
በባዛሩ ላይ ምርታቸውን ይዘው የቀረቡ አምራቾች ለኢዜአ እንደገለጹት በበዓላት ወቅት በአካባቢው የሚከፈቱ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች የበዓል ማድመቂያና ልዩ ትውስታን የሚፈጥሩ ናቸው።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፋ ዞን የማር ምርት ይዞ የቀረበው ወጣት ፋሲካ ኃብተማሪያም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ማር በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ይዞ መቅረቡን ተናግሯል።
ባዛሩ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ከአምራቹ በቀጥታ እንዲገበይ የሚያስችል ነውም ብሏል።
ቅመማቅመም እና ባልትና ውጤቶችን ይዘው በባዛሩ የቀረቡት ኤልሳ አበራ በበኩላቸው፤ በባዛሩ የተለያዩ የቅመማቅመም ውጤቶች ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ባዛሩ ለአምራቹ ከሚፈጥረው የገበያ ትስስር ባለፈ ለሸማቹም በአቅራቢያው ምርቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበረሰቡ ከወትሮ በተለየ የዘይት አቅርቦት የሚያስፈልገው በመሆኑን አጥረት እንዳይከሰት ቀደም ብሎ ከወረዳ ጀምሮ በተለያዩ ባዛርና ኤግዚቢሽኞች ላይ በስፋት ይዘን ቀርበናል የምተለው ደግሞ ወጣት ፍሬሕይወት አለንህ ነች።