ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ደረጃውን የጠበቀ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማጠናከር መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

ሮቤ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማጠናከር መሰረተ ልማቶችን እያስፋፋ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ በባሌ ሮቤ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ያስገነባውን የዋቆ ጉቱ ኤርፓርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ዛሬ አስመርቋል።


 

የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ከውጭ ሀገራት በረራዎች ባሻገር በሀገር ውስጥ ተደራሽ ለመሆን ለመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ትኩረት ሰጥቷል።

አየር መንገዱ በሀገር ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማጠናከሩ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ዘርፉን እንደሚያነቃቃም አመልክተዋል።

አየር መንገዱ የሀገሪቱን ህዝቦች ሁለንተናዊ ትስስር ለማጠናከር ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በክልል ከተሞች በመዘርጋት የበረራ አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

በባሌ ሮቤ የተገነባው የዋቆ ጉቱ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የሀገር ውስጥ በረራዎችን ለማዘመን አየር መንገዱ ከሚያከናውናቸው የማሻሻያ ስራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በአካባቢው የሚገኙ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥርን በመጨመር ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።


 

አየር መንገዱ በ22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በነገሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱን ጨምሮ በስድስት የሀገሪቱ አካባቢዎች የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ግንባታ ለተሻለ አገልግሎት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንና የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ባሌ ሮቤ ዋቆ ጉቱ ኤርፖርት 14 ሳምንታዊ በረራዎችን እንደሚያደርግ የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም