ቀጥታ፡

አየር መንገዱ እያከናወናቸው ያሉት መሰረተ ልማቶች የክልሉን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በማሳለጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው

ሮቤ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የክልሉን ንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በማሳለጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

አየር መንገዱ በባሌ ሮቤ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ያስገነባውን የዋቆ ጉቱ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃው ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት አየር መንገዱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ከግምት በማስገባት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየከናወነ ይገኛል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የክልሉን ንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በማሳለጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ተርሚናሉ በተለይም የግብርናና የቱሪዝም እምቅ ኃብት ባለቤት በሆነችው ባሌ መገንባቱ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።


 

እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያው ሥያሜ በጀግናው ጄኔራል ዋቆ ጉቱ እንዲሰየም ያደረጉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) በክልሉ መንግሥት ሥም አመስግነዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ያገኘውን የልማት አቅም በመጠቀም ለልማት መነሳሳት እንዳለበትም አቶ ሽመልስ አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንና የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ባሌ ሮቤ ዋቆ ጉቱ ኤርፖርት 14 ሳምንታዊ በረራዎችን እንደሚያደርግ የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም