ቀጥታ፡

እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ በመጠቀም እና በድህነት ቅነሳ ላይ በማተኮር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን መምራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ በመጠቀም እና በድህነት ቅነሳ ላይ በማተኮር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን መምራት እንደሚገባት አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረን ፍሪማን ገለጹ፡፡

ተንታኙ ላውረን ፍሪማን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በማስተሳሰር የቀጣናው ህዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጨምረው ገልፀዋል።

በተለይም ከሶማሊያ ጋር እየተሻሻለ የመጣውን ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማሳደግ በሀገራቱ እና በቀጣናው ያሉ ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በቅርቡ ሀገራቱ ያደረጉት ስምምነት ታሪካዊና ሰላማዊ ግንኙነታቸውን ወደ ቀደመ ቦታው ለመመለስ ማስቻሉን ነው ያብራሩት፡፡

በሀገራቱ መካከል የተጀመረው ጠንካራ ግንኙነት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ውጫዊ ኃይሎች በቀጣይም በዚሁ ተግባራቸው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አለመግባባቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአንካራ የደረሱት ስምምነት እውን መሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

በዚህም ከአለመግባባት ወደ መግባባት በመመለስ ሰላምን ማስፈን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የተጀመረውን መልካም ግንኙነት ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይም ሀገራቱ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ በጋራ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በድህነት ውስጥ የሚኖሩ የቀጣናውን ህዝቦች የኑሮ ደረጃ መሻሻል የሚያስችል በመሆኑ ትብብራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ከሶማሊያ በተጨማሪ ጅቡቲን፣ ኬንያን እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማካተት በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

በሶማሊያ ጽንፈኛውን አልሸባብ ለማስወገድ በሚደረገው ትግል የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃይል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በቅርቡ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መሪዎች መካከል ከተደረጉት ስምምነቶች በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ እንዲወጡ መጠየቁ ስህተት ነበር ሲሉም ተንታኙ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም