በቡና ልማት ምርት እና ምርታማነት መጨመሩ፣ ጥራት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የታዩ መሻሻሎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ልማት ምርት እና ምርታማነት መጨመሩ፣ ጥራት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የታዩ መሻሻሎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2017(ኢዜአ)፡- በቡና ልማት ምርት እና ምርታማነት መጨመሩ፣ በጥራት እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የታዩ መሻሻሎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው ከቡና ምርት ትመና ጋር በተያያዘ ማብራሪያ በመስጠት በጉዳዩ ላይም ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ምርት እና ምርታማነት መጨመሩ፣ በጥራት በኩል የታዩ መሻሻሎች እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝት እድገቱ የሚደነቁ ውጤቶች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው መንግስት ለቡናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የ2016/2017 የቡና ምርት ትመናን በተመለከተ የተካሄደውን ዳሰሳ በተመለከተም ለቋሚ ኮሚቴው ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል።
በዚህም የምርት ትመናው ሲካሄድ የምርምር ተቋማት፣ የባለስልጣኑ እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ የካበተ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማሳተፍ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ትመናው ሲካሄድ ተገቢውን ሳይንሳዊ ሂደት ተከትሎ፤ ዞን፣ ወረዳ እስከ አርሶ አደር ማሳ ድረስ በመውረድ ወካይ የሆኑ ናሙናዎች ተወስደው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ትንታኔውም የተለየ ጥንቃቄ ተደርጎ ሂደቱም ከስር ከስር ክትትል እየተደረገበት የተሰራ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡
ከምርት ትመናው በተጨማሪ ከእያንዳንዶቹ ዝርያዎች አንጻር ምን ያህል ተመረቱ የትስ ላይ እንገኛለን? ከበሽታ መከላከል እና ቁጥጥር፣ ከደባል ሰብሎች፣ ከቡና እደሳና ጉንደላ፣ ኩትኳቶ፣ ኮምፖስት አጠቃቀም፣ የአርሶ አደሩ የተሟላ ፓኬጅ አጠቃቀም፣ እና ሌሎች ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን እና ሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ጭምር መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም እንደሀገር ለረጅም ጊዜ በሄክታር ከ7 ኩንታል ብዙም መዝለል ሳይቻል የቆየውን ውጤት ወደ 9 ኩንታል ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም እስከ ወረዳ እና ቀበሌዎች ድረስ በመገኘት እንዲሁም ከባለስልጣኑ ጋር በየጊዜው በመገናኘት ለሚያደርገው ገንቢ ውይይት፣ ስለሚሰጠው ግብረ መልሶች እንዲሁም የስራ አቅጣጫ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስቀመጡትን ከዘርፉ የሁለት ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማሳካት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል።
በባለፉት 5 ወራት ብቻ የተገኘው ከ900 ሚሊየን ዶላር የላቀ ገቢም ዕቅዱን ከማሳካት የሚያግድ ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ምርታማነት መጨመር መቻሉን፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መጨመር፣ በጥራት በኩል በየጊዜው እየታዩ ያሉ መሻሻሎች ተደማምረው የቡናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ መልካም ውጤት እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ያለው ስራ፣ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ግብዓቶች እንዲሟሉ የሚያደግረው ጥረት መልካም መሆኑን አንስተዋል።
መሰል ተግባራት እና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲሰፉ፣ በበሽታ ቁጥጥር ላይም የበለጠ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው በኩልም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡