ቀጥታ፡

የርዕደ መሬቱ ክስተት ቀጣይነት ስለሚኖረው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል-ፕሮፌሰር አታላይ አየለ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 27/2017(ኢዜአ)፦ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ እየታየ ያለው ርዕደ መሬት ቃጣይነት ስለሚኖረው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር አታላይ አየለ (ፕ/ር) አሳሰቡ።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ርዕደ መሬት በታየባቸው አካባቢዎች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ታሳቢ ሁኔታዎች ላይ ምልከታ እያደረጉ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአፋር የስምጥ ሸለቆ አካባቢ በፈንታሌ ተራራና አካባቢው በተለይም ከመስከረም ወር ጀምሮ አልፎ አልፎ የመሬት መንቀጥቀጥ እያጋጠመ መሆኑ ይታወቃል።

የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ርዕደ መሬት ከምድር በታች የሚገኙ ዓለታማ ቁሶች ግጭት በሚፈጥሩበት ወቅት የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ያብራራሉ።

ክስተቱን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተመራማሪ እና መምህር አታላይ አየለ (ፕ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ ሳቡሬ አካባቢ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጡ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል በመጠቆም ቅልጥ ዐለቱ ባለበት እንደሚረጋጋ ካልሆነም የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው ወቅታዊ መረጃ፤ በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያላቸው ርዕደ መሬቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ይገኛሉ።

ክስተቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እየጨመሩ መምጣታቸውን በመጥቀስ በተለይም በዚህ ሳምንት በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 8 የተመዘገበ ርዕደ መሬት መከሰቱን መረጃዎች ማሳየታቸውን አመልክቷል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ክስተቶቹን በቅርብ እየተከታተሉ እንደሆነና በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት መንግስት በ 12 ቀበሌዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ መረጃ እያሰባሰበ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች መካከል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማስፈር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

ርዕደ መሬቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም