የገና በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማክበር ይገባል - የተለያዩ የክርስትና እምነት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የገና በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማክበር ይገባል - የተለያዩ የክርስትና እምነት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 26/2017 (ኢዜአ)፦የገና በዓልን በአብሮነት እና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማክበር እንደሚገባ የተለያዩ የክርስትና እምነት አባቶች ገለጹ።
ኢዜአ የገና በዓል አከባበርን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የተለያዩ የክርስትና እምነት አባቶች ገና የስጦታ በዓል በመሆኑ ያለንን በማካፈል ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የስብከት ወንጌል ኃላፊ መጋቢ አዲስ ባህረጥበብ አዱኛ እንደገለጹት ገና የአዲስ ህይወት ጅማሮ የፍቅር የመስጠትና የአብሮነት በዓል ነው።
በመሆኑም ይህ የመረዳዳት በዓል በሚከበርበት ወቅት ህዝበ ክርስትያኑ ያለውን ለሌለው በማካፈል ሊያከብረው ይገባል ብለዋል።
እንደ ገና ባሉ በዓላት የአባቶችን የአብሮነትና የመሰጣጣት እሴትን በማዳበር ለሌሎች የደስታ ምንጭ በመሆን ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባ አበራ ማኬቦ በበኩላቸው ገና የስጦታ በዓል እንደመሆኑ መጠን ክርስትያኖች ያላቸውን ለተቸገሩ ሁሉ በማካፈል የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡
ይህንን የስጦታ በዓል ህዝበ ክርስትያኑ ሲያከብር የአብሮነትንና የአለኝታነትን ስሜት በማሳየትና በማካፈል መሆን እንዳለበትም አስታውቀዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማስታወስና በማካፈል እንዲሁም ለአገር ዘላቂ ሰላም የድርሻችንን በማበርከት መሆን ይገባዋል ብለዋል።
ካለን ላይ ለተቸገረ ማካፈል የበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የህይወታችን መርህ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው።
ፍቅርና መከባበር ባለበት ጥላቻ ሊወለድ እንደማይችል የገለጹት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ፤ ለሌሎች በጎ ሐሳብን በማሰብ የእርስ በእርስ ግኑኙነትን በማጠናከር የገና በዓልን ማክበር ይገባል ብለዋል።