ቀጥታ፡

ሀገራዊ ልማትን ማሳለጥ የሚያስችል የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ ተደራሽ እየተደረገ ነው- ኢንስቲትዩቱ

ጋምቤላ፤ ታኅሣሥ 26/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ልማትን ማሳለጥ የሚያግዝ ጥራቱን የጠበቀ የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ አገልግሎቱን ለማዘመን በጋምቤላ በከተማ በ30 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ሕንፃ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል።

በዚህ ወቅት የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ፤ ተቋሙ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ አገልግሎቱን እያዘመነ መሆኑን ተናግረዋል፤

በተለይም ጥራቱን የጠበቀ፣ ወቅታዊና ተዓማኒ የአየር ትንበያ መረጃ ለመስጠት ጋምቤላን ጨምሮ በ11 ክልሎች የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎችን ገንብቶ ዝግጁ ማድረጉን ጠቅሰዋል።


 

ሕንፃዎች የተገነቡት ኢንስትቲዩቱ የሚሰጠውን የአየር ትንበያ መረጃ አገልግሎት በማዘመን የግብርናና የጤናን ጨምሮ ሌላውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማሳለጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የከፍታ አየር መመዝገቢያ ጣቢያዎችን በመገንባትና አገልግሎቱን በማስፋት በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጭምር እየተሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋልትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጤና እና ግብርናን ጨምሮ በሁሉም ልማት መስኮች ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር በአየር መዛባት ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ኢንስትቲዩቱ በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ዘርፈ ብዙ ጥረት ያመሰገኑት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለስራዎቹ መቃናት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም