የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ በስፋት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ በስፋት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ ፤ ታህሳስ 26/2017(ኢዜአ)፡- በአገሪቱ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ በስፋት ወደ ውጭ ለመላክ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ በሚፈለገው መልኩ ወደ ውጭ መላክ እንዲቻል እየተዘጋጁ ባሉ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ በአዳማ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ምርት ረጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አያሌው ሹመት በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ በስፋት ወደ ውጭ ለመላክ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ለዚህም ሰነዶች፣ መመሪያዎች፣ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጤናና የእንስሳት መድሃኒት መመሪያዎች እንዲሁም የእንሳሳት በሽታ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ላይ ትኩረት መሰጠቱንም አንስተዋል።
ይህም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ባለስልጣን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤናና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ በበኩላቸው፤ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ወደ ውጭ በስፋት ለመላክ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የእንስሳት ሀብቱን፣ ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ በባለፉት ስድስት ወራት 72 ሚሊዮን ዶዝ ክትባቶች ለክልሎች መሰራጨታቸውንም ጠቅሰዋል።