ቀጥታ፡

የገቢ አሰባሰቡን ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤት እየመጣ ነው- የገቢዎች ሚኒስትር  ዓይናለም ንጉሴ

ደሴ ፤ ታህሳስ 26/2017(ኢዜአ)፡ -በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ እየተደረገ ባለው ጥረት የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር  ዓይናለም ንጉሴ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ500 ሚሊዮን ብር በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ የቢሮ መገልገያ ህንጻ ዛሬ አስመርቋል።


 

በምርቃው ላይ ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ፤ ገቢን በስኬት ለማስፈጸም ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚህም አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና ገቢን በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአገሪቱ የሚገኙ የጉምሩክ ቅርንጫፎችን በማጠናከርና በመደገፍ ለኢትዮጵያ ሁለተናዊ እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በአገሪቱ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ እየተደረገ ባለው ጥረትም ገቢ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

በዚህም ለውጡ ሲጀመር በዓመት ከ200 ቢሊዮን ብር በታች ገቢ ይሰበሰብ የነበረው በዘንድሮው በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወር ብቻ ከ380 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።

በቀጣይም ታማኝ፣ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በመፍጠር አገሪቱ በምታመነጨው ልክ ገቢን አሟጦ በመጠቀም የማትደፈርና በኢኮኖሚ የጠነከረች አገርን ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት ሁሉም ሊደግፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ሁለተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ አሰራሩን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደራጀ፤ ከወረቀት ንክኪ ነፃና ፈጣን አገልግሎት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀዋል።

ይህም ኮንትሮባንድና ሌሎችንም ህገ-ወጥ አሰራሮችን በመከላከል የወጭና ገቢ እቃዎች ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲይዙ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉት ቅርንጫፎች የሚሰጡትን አገልግሎት ለማዘመን የሚያስችሉ የአሰራርና የህንጻዎች ግንባታ ማካሄዱን አውስተው፤ በኮምቦልቻ ከተማ በ500 ሚሊዮን ብር የተገነባው ህንፃም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአመራር አባላትና ባለሙያው ተቀናጅተው በቁርጠኝነት በመስራት የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ ደርሴ ፤ ከተማ አስተዳደሩ ለህንፃው የግንባታ ቦታ ከመስጠት ባለፈ ሌሎች ድጋፎችን ማድረጉን ጠቅሰው፤ ቀጣይም ለኮሚሽኑ ራዕይና ተልዕኮ መሳካት እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም