በሽታን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመከተል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ትኩረት ተደርጓል- ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
በሽታን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመከተል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ትኩረት ተደርጓል- ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 26/2017(ኢዜአ)፦በሽታን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመከተል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የጤና ልማት ፀረ-ወባ ማህበር በበኩሉ በመንግስት አስተባባሪነት በተለይም የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ ይገኛል ብሏል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወባን አስመልክቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያካሂደው ሳምንታዊ የውይይት መድረክ አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባጋራው መረጃ የወባ በሽታን የመከላከል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
ለዚህም ስኬት የቤት ለቤት ጉብኝት፣ የሃይማኖት መሪዎችን እና ሌሎች አደረጃጀቶችን መጠቀም የተከናወነው የግንዛቤ ፈጠራ ትልቅ እገዛ ማድረጉ ተነስቷል።
በተለይም ልዩ ትኩረት ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በወባ መከላከያ መንገዶች ዙሪያ በህዝብ ተሳትፎ የተሰራው የመከላከልና የቁጥጥር ሥራ በአብዛኛው አካባቢዎች ስርጭቱን እየቀነሰ መምጣቱ ተመላክቷል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ በመከተል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት፤ ፍትሃዊነትና ጥራትን ለማረጋገጥ የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላትና የአሰራር ስርዓቱን የማዘመን እንዲሁም ህጎችን የማፅደቅ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጤናው ዘርፍ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም ገልፀዋል።
የጤና ልማት ፀረ-ወባ ማህበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አክሊሉ ጌትነት ለኢዜአ እንደገለጹት በስነ-ተዋልዶ ጤና፣ ተላላፊ በሆኑና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መከላከል፣ መቆጣጠርና ለድንገተኛ በሽታዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ ማህበሩ ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው የማህበሩ ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የወባ ስርጭትን ለመከላከል ማህበረሰብ ተኮር የወባ መከላከል ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም ክልል ለመተግበር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ማህበሩ በልማት ቀጣናዎች አካባቢ የሚሰማሩ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞችና ሌሎች ለወባ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ ወባ ታክሞ የሚድንና ሊከላከሉት የሚችሉት በሽታ መሆኑን ተገንዝቦ የበሽታው መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በአግባቡ መተግበር እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።
ማህበሩ ከመንግስት ጋር በመሆን በግጭት አካባቢ ያሉና የግብዓት እጥረት ላጋጠማቸው ጤና ተቋማት አስፈላጊ ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የህክምና ግብዓቶችን የማጓጓዝ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ባለፉት አስር ዓመታት የወባ በሽታ ዋነኛ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።