የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተመራጭነትና ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል በሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተመራጭነትና ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል በሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው
ታኅሣሥ 26/2017(ኢዜአ )፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተመራጭነትና ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል በሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ማፍራት ላይ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
አየር መንገዱ በበረራ መስተንግዶ ሙያ ለመቀጠር የተመለመሉ ወጣቶችን የአየር መንገዱ ባለሙያዎችን አሰማርቶ በተለያዩ የሀገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተና እየሰጠ ነው።
በዚህም በአዳማ፣ በጋምቤላ፣ በጅማ፣ በአሶሳ፣ በድሬዳዋ፣ በሰመራና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናው እየተሰጠ ነው።
በአየር መንገዱ የኢንዱስትሪ ግኑኝነትና የሰው ሀብት ፖሊሲ ክፍል ማናጀር እና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የፈተናው አስተባባሪ አቶ ምህረቱ ቡርሳሞ እንደገለፁት፤ አየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተመራጭነትና ተወዳዳሪ ነት ለማስቀጠል በሰለጠነ የሰው ሃይል ልማት ላይ አበክሮ እየሰራ ነው።
በዚህም በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የአቪዬሺን ባለሙያዎች ምልመላ በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት እየሰራ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም በሀገሪቷ 18 ዩኒቨርሲቲዎች ከ 20 ሺ ለሚበልጡ ሰዎች የምልመላ ፈተና እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓለም የአቪየሺን ዘርፍ የስልጠና አድማሱን በማስፋት በተለይም በአብራሪነትና በበረራ አስተናጋጅነት ሙያተኞችን ለማፍራት ከጋቦን፣ ማላዊና ናይጄሪያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተሰጠው ፈተና የሰው ሀይል አስተዳደር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ራምሲስ ጅራ በዩኒቨርስቲዎች የሚሰጠው ፈተና አየር መንገዱ ለያዘው የሰለጠነ የሰው ሀይል ማፍራት ግብ እንዲሳካ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፈተናው አስተባባሪ ትዕግስት ከፍያለው በበኩላቸው የሀገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ ባለሙያዎችን በማፍራት ህብረ ብሔራዊነቱን አጥብቆና ታላቅነቱን አፅንቶ በመገስገስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።