ቀጥታ፡

በበዓላት ወቅት አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል- አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 26/2017)ኢዜአ)፦ በበዓላት ወቅት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ታዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በበዓል ወቅት የሚስተዋለውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ዘርፈ ብዙ የቅደመ ዝግጅት ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም ለገና እና ጥምቀት በዓላት የሀይል እጥረትና መቆራረጥ እንዳይከሰት፣ መስመሮችን የመጠገን፣ ትራንስፎርመሮችን የመፈተሽና ችግር ያለባቸውን የማስተካከል ስራ ተስርቷል ብለዋል፡፡

የኃይል መቆራረጥ ቢከሰት እንኳን በፍጥነት መጠገን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡ በበዓላት ወቅት ጥንቃቄ በተሞላበት የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን አጠቃቀም ማረጋገጥና በቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ መገልገያ ቁሳቁሶችን በአንድ ጊዜ ባለመጠቀም መገልገል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም