ቀጥታ፡

ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ የምግብ ዘይት ምርቶች ወደ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰራጩ ነው - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ ለመጪው የገናና የጥምቀት በዓላት ፍጆታ የሚውሉ የምግብ ዘይት ምርቶች ወደ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰራጩ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።


 

በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ በነበሩ ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን አቅርቦት ለማሻሻል ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን እያንዳንዳቸው 17 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በጥቅሉ 34 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ወደ ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች እየተሠራጨ ይገኛል ብለዋል፡፡

የበዓል መዳረሻ ወቅት መሆኑን ተከትሎ የሠብልና አትክልት፣ የቁም እንስሳት፣ የእንስሳት ተዋፅኦ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በዩኒየኖች፣ ባዛሮችና መሠል የግብይት አማራጮችን በመጠቀም ለህብረተሠቡ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡


 

ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ለህብረተሠቡ ተደራሽ ለማድግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ነጋዴዎች በሃላፊነት ምርቶችን በመደበኛው ዋጋ እንዲያቀርቡ በተጨማሪም የመንግስት ባለድርሻ አካላት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም