ኮሚሽኑ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ጠቃሚ ግብአቶች ማሰባሰቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ጠቃሚ ግብአቶች ማሰባሰቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ጠቃሚ ግብአቶች ማሰባሰቡን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ባሉ እና በቀጣይ ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ስራዎች ላይ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት፣ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በአካል በመገኘት ያላቸውን አጀንዳ እና ጥያቄዎች ለማዳመጥ እና ለማሰባሰብ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሚሲዮኖች በሚፈልጋቸው ትብብሮች ላይ ገለጻ ቀርቧል።
ሀገራዊ ምክክር ግጭትን በማስወገድ ረገድ ያለው ሚና የላቀ እንደመሆኑ መጠን ምክክሩ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያለው ሚናም ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አካታች፣ ነጻ እና ገለልተኛ በመሆን በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር ምክክር ሲያደረግ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን ከውይይቶቹም ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ መቻሉም ተጠቅሷል።
በገለጻው ላይ በመመስረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሚሲዮን መሪዎች እና ዲፕሎማቶች ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽነሮች ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታለ።